Home » News Events » በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት ሊከሰቱ የሚችሉ ተጽዕኖዎችን መቋቋም የሚያስችል ዝግጅት ተደርጓል - የኢትዮጵያ አደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን

በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት ሊከሰቱ የሚችሉ ተጽዕኖዎችን መቋቋም የሚያስችል ዝግጅት ተደርጓል - የኢትዮጵያ አደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን

ጥር 07/2016ዓ.ም

በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት ሊከሰቱ የሚችሉ ተጽዕኖዎችን መቋቋም የሚያስችል ዝግጅት ተደርጓል - የኢትዮጵያ አደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን

መጪዎቹ ወራት በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት ሊከሰቱ የሚችሉ ተጽዕኖዎችን መቋቋም የሚያስችል ዝግጅት ማድረጉን የኢትዮጵያ አደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን አስታወቀ።

የኢትዮጵያ አደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን ምክር ቤት ላለፉት አራት ወራት ተግባራዊ ሲደረግ የቆየውን የአስቸኳይ ጊዜ እቅድ አፈጻጸም የፌዴራልና የክልል ከፍተኛ አመራሮች በተገኙበት ገምግሟል።

በመድረኩም ባለድርሻ ተቋማት ሲያከናውኑት የቆዩት ቅንጅታዊ አሰራር ቀርቦ ውይይት ተደርጎበታል፡፡

የኢትዮጵያ አደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን ኮሚሽነር አምባሳደር ሽፈራው ተክለማሪያም(ዶ/ር) በዚሁ ወቅት፤ ብሔራዊ የአደጋ ስጋት አመራር ምክር ቤት ላለፉት አራት ወራት ሰፊ ስራዎችን ሲያከናውን መቆየቱን ገልጸዋል።

ስራዎቹም በዋናነት በሀገሪቱ ሊያጋጥሙ የሚችሉ የተፈጥሮ አደጋዎችን መሰረት ያደረጉ መሆናቸውን ነው የተናገሩት፡፡

በመድረኩም ባለፉት አራት ወራት የተከናወኑ ስራዎች አፈጻጸም ላይ ውይይት መደረጉን ጠቅሰው፤ በዚህም ባለድርሻ ተቋማት በእቅዳቸው መሰረት የተሻለ ስራ ማከናወናቸውን ገልጸዋል፡፡

በመጪው የበልግ ጊዜም የበልግ ዝናብ ተጠቃሚ በሆኑት የሀገሪቱ አካባቢዎች የአየር ንብረት ለውጥ ሊያስከትል የሚችለውን ተጽእኖ ለመቋቋም በምክር ቤቱ በኩል ዝግጅቶች መደረጉን ጠቁመዋል።

ካለፈው ሀምሌ ወር ጀምሮ በመንግስት በኩል 11 ቢሊዮን ብር እንዲሁም በአጋር ድርጅቶች 4 ቢሊዮን ብር የሚያወጣ ሰብዓዊ ድጋፍ በችግር ውስጥ ለሚገኙ የማህበረሰብ ክፍሎች ተደራሽ መደረጉን አስታውቀዋል።

በመጪዎቹ ጥር፣ የካቲትና መጋቢት ወራትም 6 ነጥብ 6 ሚሊዮን ለሚሆኑ ዜጎች ሰብዓዊ ድጋፍ ተደራሽ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑንም ኮሚሽነሩ ጨምረው ገልጸዋል፡፡

ይህም በገንዘብ ሲተመን ወደ 9 ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር የሚጠጋ ሀብት መሆኑን ነው የተናገሩት፡፡

ከምግብ እህሎች ጋር ተያይዞም በሚቀጥሉት 3 ወራት 1ነጥብ 1 ሚሊዮን ኩንታል የቅድሚያ ቅድሚያ ለሚያስፈልጋቸው የማህበረሰብ ክፍሎች የሚሰራጭ ሲሆን፤ ከ500 ሺህ ኩንታል በላይ የሚሆነው በኮሚሽኑ በኩል እንደሚቀርብ ታውቋል፡፡

ቀሪው በአጋር ድርጅቶች በኩል የሚቀርብ ይሆናል ሲሉም ገልጸዋል።

            

Wednesday, January 17, 2024