Home » News Events » ኮሚሽኑ የውሃ አቅርቦት እጥረትን ለማቃለልና የተስተጓጎሉ ተግባራትን ወደ ስራ ለማስገባት ድጋፍና ክትትል ያደርጋል::

ኮሚሽኑ የውሃ አቅርቦት እጥረትን ለማቃለልና የተስተጓጎሉ ተግባራትን ወደ ስራ ለማስገባት ድጋፍና ክትትል ያደርጋል::

ኮሚሽኑ የውሃ አቅርቦት እጥረትን ለማቃለልና የተስተጓጎሉ ተግባራትን ወደ ስራ ለማስገባት ድጋፍና ክትትል ያደርጋል::

የአደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት የተከሰተውን የውሃ አቅርቦት እጥረት ለማቃለልና የተስተጓጎሉ ተግባራትን ወደ ስራ ለማስገባት ድጋፍና ክትትል እንደሚያደርግ ኮሚሽነር አምባሳደር ሽፈራው ተክለማርያም(ዶ/ር) አስታወቁ።

የአደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽነር አምባሳደር ሽፈራው(ዶ/ር) በአፋር ክልል ኮሪ ወረዳ ሙስሌ ቀበሌ ተገኝተው ድርቅ የተከሰተበትን አካባቢ በመጎብኘት ከህብረተሰቡ ጋርም ተወያይተዋል።

አምባሳደር ሽፈራው(ዶ/ር) እንደገለጹት፤ በአሁኑ ወቅት የአየር ንብረት ለውጥ በአገራችን በተለያዩ አካባቢዎች በድርቅ ወይም በጎርፍ መልክ ጉዳት እያስከተለ ይገኛል።

አፋር ክልል ኮሪ ወረዳ ላለፉት 12 ወራት ዝናብ ባለመዝነቡ የአካባቢው ነዋሪዎች ተጎጂ መሆናቸውን ጠቁመው፤ በቦቴ የተጀመረው የውሃ አቅርቦት ተጠናክሮ እንዲቀጥል ድጋፍ እንደሚደረግ አመልክተዋል።

በአካባቢው የውሃ አቅርቦት በመስተጓጎሉ የትምህርት የጤና እና የእንሰሳት መኖ ችግር ማጋጠሙን መረዳታቸውን ጠቁመው፤ በአካባቢው ላይ በአካል ተገኘተው ድርቁ ወደ ረሐብ ተቀይሮ በሰው ህይወት ላይ ጉዳት ያለማድረሱን ማረጋገጣቸውን አብራርተዋል።

ድርቅ መከሰቱን በምክንያትነት በማቅረብ ህብረተሰቡ እጁን አጣጥፎ ያለመቀመጡን ያመለከቱት አምባሳደር ሽፈራው፤ የቤት እንስሳትን ወደ ሌላ አካባቢ በማጓጓዝ የማቃለያ መንገዶችን ተግባራዊ ማድረጉን በመልካም ተሞክሮነት ጠቅሰዋል።

በተለያዩ አጋር ተቋማት ተሰርተው ወደ ስራ ያልገቡ የውሃ ተቋማት ወደ ሥራ እንዲገቡ የመደገፍና የመከታተል ተግባር እንደሚከናወንም ተናግረዋል።

በውሀ ምክንያት ተቋርጠው የቆዩ ትምህርት ቤቶችም ሆኑ የምገባ መርሃ ግብሮች ወደ ስራ እንዲገቡ እንደሚደረግም ገለጸዋል።

የክልሉ የአደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽነር መሐመድ ሁሴን በበኩላቸው፤ ቀደም ብሎ በክልሉ በ6 ዞኖችና በ15 ወረዳዎች የዳሰሳ ጥናት ተካሄዷል።

በዳሰሳ ጥናቱ መሠረት 590ሺህ ነዋሪዎች በቀጥታ ተጎጂዎች እንደሆኑ መለየቱን አመልክተው፤ 413 ሺህ ህዝብ የአስቸኳይ ጊዜ የምግብና የውሃ እንዲሁም የሌሎች ድጋፍ ፍላጎቶች መኖራቸውን አስታውቀዋል።

ይህንንም መሠረት በማድረግ ከተለያዩ አጋር አካላትና የመንግስት አካላት ጋር በመተባበር ሰፊ የአደጋ ምላሽና የድርቅ ምላሽ ስራዎች መከናወናቸውን ተናግረዋል።

ላለፉት ስድስት ወራት የፌዴራል የክልልና የአጋር አካላትን አቅም በመጠቀም ለ500 ሺህ ህዝብ ተከታታይ የሆነ የእርዳታ እህል የቅድሚያ ቅድሚያ ለሚያስፈልጋቸው የማህበረሰብ ክፍሎች መዳረሱን አብራርተዋል።

እንደ ክልል የመጨረሻውን አማራጭ በመጠቀም ውሀና ዝናብ አጠር በሆኑት ስፍራዎች ከ17 በላይ የውሃ ቦቴዎችን በመመደብ በስፋት የውሃ አቅርቦት ላይ እየተሰራ መሆኑንም አስታውቀዋል።

የኮሪ ወረዳ አስተዳዳሪ አቶ አባስ ሐሮ በወረዳዋ ውስጥ አንድም ግብረ ሰናይ ድርጅት አለመኖሩን ጠቅሰው፤ “ህዝባችንን በዘላቂነት ልንደግፈው ይገባል”።

በወረዳዋ ውስጥ የነበረችው አንዲት የውሀ ቧንቧ መቋረጧን ያስታወሱት አስተዳዳሪው፤ ለአራት ቀበሌ ማገልገል እንደምትችልና አገልግሎቷ እንዲጀመር ጠይቀዋል።

የወረዳው እንሰሳት እርሻና ተፈጥሮ ሀብት ፅህፈት ቤት ሃላፊ አቶ አደን መሐመድ በበኩላቸው፤ ህዝባቸው በውሃ እጦት ምክንያት ከአካባቢያቸው ርቀው እንደሚገኙ ገልጸዋል።

በዕለቱ በኢትዮጵያ የዓለም ምግብ ኘሮግራም ዋና ዳይሬክተር ሚስተር ክሪስና የአፋር ኦቻ ተወካይና ሌሎች የመንግስትና መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ኃላፊዎች በጉብኝቱ ተሳትፈዋል።

          

 

Thursday, February 8, 2024