ጥር 27/2016ዓ.ም
የድርቅ አደጋን ለፖለቲካ አላማ ማስፈፀሚያ ለማዋል የሚደረግ ጥረት በፍፁም ተገቢ አይደለም- የአደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽንአካባቢዎች የተከሰተውን ድርቅ ለፖለቲካ አላማ ማስፈፀሚያ ለማዋል የሚደረግ ጥረት ተገቢ ያልሆነና በፍፁም ተቀባይነት የሌለው መሆኑን የአደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን ኮሚሽነር ዶክተር ሽፈራው ተክለማርያም ገለጹ።
ለተከሰተው የድርቅ አደጋ መንግስት አፋጣኝ ሰብአዊ ድጋፍና የተቀናጀ ምላሽ እየሰጠም ይገኛል ብለዋል።
የአደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽነር ዶክተር ሽፈራው ተክለማርያም ድርቅ በተከሰተባቸው አካባቢዎች ሰብአዊ ድጋፍን ጨምሮ ሌሎች እየተከናወኑ ያሉ ስራዎችን በተመለከተ ለኢዜአ ማብራሪያ ሰጥተዋል።
ኮሚሽነሩ በማብራሪያቸው አሁን ላይ 6 ነጥብ 6 ሚሊዮን ዜጎች የሰብአዊ ድጋፍ የሚሹ መሆኑን ገልጸው፤ መንግስት በተቀናጀ መልኩ ምላሽ ለመስጠት እየሰራ ይገኛል ብለዋል።
የሰብአዊ ድጋፍ የሚሰጡ አካላት ባለፈው አንድ ዓመት ከግማሽ የድጋፍ ምላሻቸው የተቀዛቀዘ ስለነበር ከ70 በመቶው በላይ በመንግስት አቅም መሸፈኑን ገልጸዋል።
ከሰብአዊ ድጋፍ ፍላጎት አንጻር ባለፈው አመትም የተገኘው 33 በመቶ ብቻ መሆኑን አስታውሰው መንግስት ባለፉት ስድስት ወራት በ 11 ቢሊዮን ብር ወጭ 1 ነጥብ 3 ሚሊዮን ኩንታል እህል ገዝቶ አከፋፍሏል ብለዋል።
እርዳታ ሰጭዎች ያለምንም ማስጠንቀቂያ ድጋፍ ባቆሙበት ወቅት መንግስት ተጨማሪ ሀብት በመመደብ ዜጎቹን መታደግ መቻሉን አስታውሰው በቀጣይም ድጋፍ ለሚሹ ዜጎች ድጋፍ ለማድረግ በቂ ዝግጅት ተደርጓል ብለዋል።
በኢትዮጵያ የተከሰተው ድርቅ እንጂ ርሀብ አለመሆኑን የገለጹት ኮሚሽነሩ በዓለም አቀፍ ተቋማት ጥናት እና በባለድርሻ አካላት ፈጣን ዳሰሳም ርሃብ አለመሆኑን ለማረጋገጥ ተችሏል ብለዋል።
በመሆኑም የተከሰተውን ድርቅ ለፖለቲካ አላማ ማስፈፀሚ ለማዋል የሚደረግ ጥረት ተገቢ ያልሆነና በፍፁም ተቀባይነት የሌለው መሆኑን አስረድተዋል።
የድርቅ አደጋውን ተከትሎ የፌደራል መግስት የሰብአዊ ድጋፍና ፈጣን ምላሽ እየሰጠ መሆኑን ጠቅሰው በዚህ ረገድ የክልሎችም ተሳትፎ ሊጠናከር ይገባል ብለዋል።
በመንግስት እየተደረጉ ያሉ ድጋፎች በትክክል ድጋፍ ለሚሹ ወገኖች መድረሱን የማረጋገጥ ስራ በቅንጅት ሊሰራ እንደሚገባ አሳስበዋል።
Copyright © 2024 Disaster Risk Management Commission