Home » News Events » ድሬዳዋ እና አዲስ አበባ ከተማ አስተዳደርን ጨምሮ ስድስት ክልሎች የሰብዓዊ ድጋፍ ጥያቄን በራሳቸው መሸፈን የሚያስችል አቅም ፈጥረዋል::

ድሬዳዋ እና አዲስ አበባ ከተማ አስተዳደርን ጨምሮ ስድስት ክልሎች የሰብዓዊ ድጋፍ ጥያቄን በራሳቸው መሸፈን የሚያስችል አቅም ፈጥረዋል::

ሐምሌ 1 ቀን 2016 ዓ.ም

ድሬዳዋ እና አዲስ አበባ ከተማ አስተዳደርን ጨምሮ ስድስት ክልሎች የሰብዓዊ ድጋፍ ጥያቄን በራሳቸው መሸፈን የሚያስችል አቅም ፈጥረዋል::

***********************

ድሬዳዋ እና አዲስ አበባ ከተማ አስተዳደርን ጨምሮ ስድስት ክልሎች የሰብዓዊ ድጋፍ ጥያቄን በራሳቸው መሸፈን የሚያስችል አቅም መፍጠራቸውን የኢትዮጵያ አደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽነር አምባሳደር ሽፈራው ተክለማርያም(ዶ/ር) ተናገሩ።

ኢትዮጵያን ከተረጂነት ማላቀቅ የብሔራዊ ክብር ጉዳይ በመሆኑ ለተፈጥሮ እና ሰው ሰራሽ አደጋዎች በራስ አቅም ምላሽ መስጠት ላይ ትኩረት ተደርጎ እየተሰራ መሆኑንም ገልፀዋል፡፡

ኮሚሽነር አምባሳደር ሽፈራው ተክለማርያም(ዶ/ር) ለኢዜአ እንደገለጹት፤ ሀገርን ከተረጂነት ማላቀቅ የሚያስችል የቅድመ-አደጋ መከላከል፣ የአደጋ ወቅትና ከአደጋ በኋላ በራስ አቅም ምላሽ መስጠት የሚያስችል አሠራር እየተዘረጋ መሆኑን አስታውቀዋል።

ሰብዓዊና ቁሳዊ ድጋፍ ለሚያስፈልጋቸው ዜጎችም በዓመት ሁለት ጊዜ በሚካሄድ የዳሰሳ ጥናት ተጋላጭነትን ማስቀረት የሚያስችል የልማታዊ ሴፍቲኔት ድጋፍ ሥርዓት እየቀረበ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

ረጂ ድርጅቶችም የዕለት ደራሽ ድጋፍ መስጠት ሰብዓዊነት ቢሆንም ድጋፍ የሚሹ ወገኖች በዘላቂ የልማት ግብ ተሰማርተው እራሳቸውን በሚያቋቁሙበት የሥራ መስክ መደገፍ እንደሚጠበቅባቸው አስገንዝበዋል።

ድሬዳዋ እና አዲስ አበባ ከተማ አስተዳደርን ጨምሮ ስድስት ክልሎች የሰብዓዊ ድጋፍ ጥያቄዎችን በራሳቸው መሸፈን የሚያስችል አቅም መፍጠራቸውን አብራርተዋል፡፡

ግጭት ለነበረባቸው ትግራይ፣ አማራና አፋር ክልሎች ድጋፍ እየቀረበ መሆኑን ጠቁመው፤ በቀጣይም ሁሉም ክልሎች ራሳቸውን እንዲችሉ ይደረጋል ብለዋል።

በመጠለያ ጣቢያ ለሚገኙ ዜጎች ሰብዓዊ ድጋፍ ቅድሚያ ተሰጥቶ እየቀረበ ነው ያሉት ኮሚሽነሩ፤ ጎን ለጎንም ተፈናቃይ ዜጎች ወደ መኖሪያ ቀያቸው በመመለስ በዘላቂነት ለማቋቋም እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

በተፈጥሮ እና በሰው ሰራሽ አደጋዎች ምክንያት ተፈናቅለው በመጠለያ ጣቢያ የሚገኙ ዜጎች አብዛኞቹ ወደ መኖሪያ ቀያቸው እንዲመለሱ መደረጉን ገልፀዋል።

ኢትዮጵያን ከተረጂነት ማላቀቅ የብሔራዊ ክብር ጉዳይ በመሆኑ ለተፈጥሮ እና ሰው ሰራሽ አደጋዎች በራስ አቅም ምላሽ መስጠት ላይ ትኩረት ተደርጎ እየተሰራ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡

ከተረጂነት ለመላቀቅም ዜጎች በሁሉም የልማት መስክ በመረባረብ ምርታማነትና በራስ አቅም የመደጋገፍ ባህልን ማጎልበት እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

ኢትዮጵያን የሚመጥን የአደጋ ስጋት ሥራ አመራር ፖሊሲ በመቅረጽ የአደጋ መከላከልና መቆጣጠር የፈንድና ክምችት አቅምን ማጎልበት የሚያስችሉ አሠራሮች እየተዘረጉ መሆኑንም ጠቅሰዋል።

ለዚህም የተፈጥሮ እና ሰው ሰራሽ አደጋዎችን በተሻለ አቅም ምላሽ መስጠት የሚችል ተቋም ለማደራጀት ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን አስታውቀዋል።

የአደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን ከክልሎች ጋር በመሆን ምግብና ምግብ-ነክ ያልሆኑ የስትራቴጂክ መጠባበቂያ ክምችት ፍላጎት ልየታ መደረጉን ገልፀዋል።

ለዚህም ከ500 ሺህ የመጠባበቂያ ክምችት ውስጥ 80 ሺህ ሄክታር መሬትን በማልማት 150 ሺህ የሚሆነው በፌዴራል ቀሪውን ደግሞ በክልሎች መሸፈን የሚያስችል ስሌት በማድረግ ወደ ሥራ መገባቱን ተናግረዋል።

የአደጋ ስጋት የብሔራዊ ደኅንነት ጉዳይ በመሆኑ የእሳትና ድንገተኛ አደጋን ጨምሮ የቅጽበታዊ አደጋን መከላከል የሚያስችሉ ተቋማትን ለማደራጀት ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል።

ተረጂነት ክብርን የሚያዋርድና የተሟላ ነፃነት የሚያጎድል መሆኑን ጠቁመው፤ ለዚህም ኢትዮጵያ ሰፊ የተፈጥሮ ጸጋና አምራች የሰው ኃይል ያላት ሀገር ሆና ሳለ በተረጂነት ላይ ጥገኛ መሆን እንደማይኖርባት አንስተዋል።

የአንድ ሀገር ሕዝብ የሚገነባውንም ሆነ የሚጠቀምበትን በራሱ አቅም ማምረት ካልቻለ ነፃነቱ የተጓደለ በመሆኑ ከተረጂነት ወደ ምርታማነት መሸጋገር አስፈላጊ ጉዳይ መሆኑን አጽንዖት ሰጥተዋል።

Monday, July 8, 2024