Home » News Events » “የአደጋ ስጋት ስራ አመራር ፖሊሲ የሀገር ብሔራዊ ደህንነት በመሆኑ የዜጎችን ክብር በሚያስጠብቅ መልኩ ተግባራዊ መደረግ አለበት” አምባሳደር ሽፈራው ተ/ማርያም( ዶ/ር)

“የአደጋ ስጋት ስራ አመራር ፖሊሲ የሀገር ብሔራዊ ደህንነት በመሆኑ የዜጎችን ክብር በሚያስጠብቅ መልኩ ተግባራዊ መደረግ አለበት” አምባሳደር ሽፈራው ተ/ማርያም( ዶ/ር)

ቀን፡-  ሐምሌ 01/2016ዓ.ም

የአደጋ ስጋት ስራ አመራር ፖሊሲ የሀገር ብሔራዊ ደህንነት በመሆኑን የዜጎችን ክብር በሚያስጠብቅ መልኩ ተግባራዊ መደረግ አለበት::
 
አዲስ አበባ፤ ሰኔ 28/2016(ኢዜአ)፦ የአደጋ ስጋት ስራ አመራር ፖሊሲ የሀገር ብሔራዊ ደህንነት ጉዳይ መሆኑንና የዜጎችን ክብር በሚያስጠብቅ መልኩ ተግባራዊ መደረግ እንዳለበት በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውጭ ግንኙነትና ሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አሳሰበ።
የኢትዮጵያ አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን ሱሉልታ በሚገኘው የአፍሪካ አመራር ልህቀት አካዳሚ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ለውጭ ግንኙነትና ሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አባላት በአደጋ ስጋት ስራ አመራር ፖሊሲና በአደጋ ስጋት ስራ አመራር ረቂቅ አዋጅ ዝግጅትን አስመልክቶ ገለጻ አድርጓል።
የኢትዮጵያ አደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽነር አምባሳደር ሽፈራው ተክለማርያም (ዶ/ር)፥ አደጋ ስጋት ስራ አመራር ፖሊሲን በየካቲት ወር 2016 ዓ.ም በማጽደቅ የማቋቋሚያ ረቂቅ አዋጅ ተዘጋጅቷል ብለዋል።
 
በዚህም ፖሊሲውና ረቂቅ አዋጁም በኢትዮጵያ የሚከሰቱ ሰው ሰራሽና የተፈጥሮ አደጋዎችን በራስ አቅም ምላሽ በመስጠት ብሔራዊ ደህንነትና ክብርን ለማስጠበቅ ያግዛሉ ብለዋል።
ረቂቅ አዋጁ ሲጸድቅም የአደጋ ስጋት መጠባበቂያ ፈንድ፣ ስትራቴጂክ መጠባበቂያ ክምችትና የድንገተኛ አደጋዎች አገልግሎት ተጠሪ ተቋማት የሚደራጁ መሆኑን አስታውቀዋል።
በተለይም የአደጋ ስጋት መጠባበቂያ ፈንድ ሲቋቋም አደጋን በራስ አቅም ምላሽ የመስጠት አቅም በማጎልበት የሀገርን ሉዓላዊነት እና ክብር ለማስጠበቅ ጉልህ ፋይዳ እንደሚኖረው አስረድተዋል።
 
በዚህም ዜጎችን በቅድመ አደጋ፣ በአደጋና ከድሕረ አደጋ የሚከሰቱ የተፈጥሮና ሰው ሰራሽ ችግሮችን ምላሽ ለመስጠት መሰረታዊ ለውጥ የሚያመጣ መሆኑን ተናግረዋል።
የሀገርን ነፃነት የተሟላ የሚያደርግ፣ በጠባቂነት እና ጥገኝነት ላይ የተንጠለጠለውን የአደጋ ምላሽ አሰጣጥ ሂደት በመቀየር የዜጎችን ክብር የሚያስጠብቅ አሰራር ሲሰፈን ነው ብለዋል።
በኢትዮጵያ አደጋ ስጋት አመራር የፕሮግራሞች ማስተባበሪያ ዘርፍ ምክትል ኮሚሽነር ነሲቡ ያሲን፥ የአደጋ ስጋት ስራ አመራር ፖሊሲን ይዘትና ምንነት ለውይይነት መነሻነት አቅርበዋል።
ፖሊሲው የኢትዮጵያን የልማት፣ ዕድገትና ብልጽግና እንዲሁም ዓለም አቀፍ ለውጦችን ተከትሎ ሊከሰቱ የሚችሉ ስጋቶችን ምላሽ መስጠት በሚያስችል መልኩ ተዘጋጅቶ ስራ ላይ መዋሉን አስረድተዋል።
በዚህም በገጠርም ሆነ ከተማ ማንኛውንም አይነት የተፈጥሮና ሰው ሰራሽ አደጋ በራስ አቅም ምላሽ መስጠት የሚያስችል የአሰራር ስርዓት መሆኑን አመላካች ነው ብለዋል።
በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውጭ ግንኙነትና ሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ምክትል ሰብሳቢ፤ ፈትሂ መህዲ(ዶ/ር)፤ የአደጋ ምላሽ የሀገርን ብሔራዊ ደህንነት የማስጠበቅ መሰረታዊ ጉዳይ ነው ብለዋል።
 
ለዚህም የኢትዮጵያን የአደጋ ስጋት ስራ አመራር ፖሊሲ የሀገር ብሔራዊ ጥቅም እና የዜጎችን ክብር በሚያስጠብቅ መልኩ ተግባራዊ ማድረግ እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል።
የሀገርን ብሔራዊ ደህንነት እና የዜጎችን ክብር በማስጠበቅ ከተረጂነት መላቀቅ በሚያስችል መልኩ ብሔራዊ ንቅናቄ የሚፈልግ ጉዳይ መሆኑን ገልጸዋል።
በኢትዮጵያ በ2030 ዓ.ም ለአደጋ ስጋት የማይበገር ማህበረሰብን ለመገንባት በሚደረገው ጥረት የአደጋ ስጋት ስራ አመራር ፖሊሲ በተፈጥሮና ሰው ሰራሽ ምክንያት የሚያጋጥሙ ችግሮችን በራስ አቅም ምላሽ ለመስጠት መሰረት እንደሚሆን ተገልጿል።
    

 

Monday, July 8, 2024